5 MAİDE

 • 5:1

  እናንተ ያመናችሁ ሆይ! በቃል ኪዳኖች ሙሉ፡፡ በእናንተ ላይ የሚነበበው ብቻ ሲቀር፡፡ የግመል፣ የከብት፣ የበግና የፍየል እንስሳዎች እናንተ በሐጅ ሥራ ላይ ኾናችሁ ማደንን የተፈቀደ ሳታደረጉ ለእናንተ ተፈቀዱ፡፡ አላህ የሚሻውን ይፈርዳል፡፡

 • 5:2

  እናንተ ያመናችሁ ሆይ! የአላህ (ክልክል ያደረጋቸውን) ምልክቶች የተፈቀዱ አታድርጉ፡፡ የተከበረውንም ወር በመጋደል አትድፈሩ፡፡ ወደ መካ የሚነዱትን መስዋዕትና የሚታበቱባቸውንም ገመዶች ከጌታቸው ችሮታንና ውዴታን ፈልገው ወደ ተከበረው ቤት አሳቢዎችንም ሰዎች (አትንኩ)፡፡ ከሐጅም ሥራ በወጣችሁ ጊዜ ዐድኑ፡፡ ከተከበረው መስጊድ ስለከለከሉዋችሁ ሰዎችን መጥላትም (በነሱ ላይ) ወሰን እንድታልፉ አይገፋፋችሁ፡፡ በበጎ ነገርና አላህን በመፍራትም ተረዳዱ፡፡ ግን በኃጢአትና ወሰንን በማለፍ አትረዳዱ፡፡ አላህንም ፍሩ፡፡ አላህ ቅጣተ ብርቱ ነውና፡፡

 • 5:3

  በክት፣ ፈሳሽ ደምም፣ የእሪያ (አሣማ) ሥጋም፣ በርሱ ከአላህ (ስም) ሌላ የተነሳበትም፣ የታነቀችም፣ ተደብድባ የተገደለችም፣ ተንከባላ የሞተችም፣ በቀንድ ተውግታ የሞተችም፣ ከርሷ አውሬ የበላላትም (ከእነዚህ በሕይወት ደርሳችሁ) ያረዳችሁት ብቻ ሲቀር ለጣዖታትም የታረደው በአዝላምም ዕድልን መፈለጋችሁ በእናንተ ላይ እርም ተደረገ፡፡ ይህ ድርጊት አመጽ ነው፡፡ ዛሬ እነዚያ የካዱት ከሃይማኖታችሁ ተስፋ ቆረጡ፡፡ ስለዚህ አትፍሩዋቸው፡፡ ፍሩኝም፡፡ ዛሬ ሃይማኖታችሁን ለናንተ ሞላሁላችሁ፡፡ ጸጋዬንም በናንተ ላይ ፈጸምኩ፡፡ ለእናንተም ኢስላምን ከሃይማኖት በኩል ወደድኩ፡፡ በረኃብ ወቅት ወደ ኃጢአት ያዘነበለ ሳይሆን (እርም የኾኑትን ለመብላት) የተገደደ ሰውም (ይብላ)፡፡ አላህ መሓሪ አዛኝ ነውና፡፡

 • 5:4

  ለእነርሱ ምን እንደተፈቀደላቸው ይጠይቁሃል፡፡ በላቸው፡- «ለእናንተ መልካሞች ሁሉና እነዚያም ከአዳኞች አሰልጣኞች ኾናችሁ ያስተማራችኋቸው (ያደኑት) ተፈቀደላችሁ፡፡ አላህ ከአስተማራችሁ ዕውቀት ታስተምሯቸዋላችሁ፡፡ ለእናንተም ከያዙላችሁ ነገር ብሉ፡፡ በርሱም ላይ የአላህን ስም አውሱ፡፡ አላህንም ፍሩ አላህ ምርመራው ፈጣን ነውና፡፡»

 • 5:5

  ዛሬ መልካሞች ሁሉ ለናንተ ተፈቀዱ፡፡ የእነዚያም መጽሐፍን የተሰጡት ሰዎች ምግብ (ያረዱት) ለእናንተ የተፈቀደ ነው፡፡ ምግባችሁም ለነሱ የተፈቀደ ነው፡፡ ከምእመናት ጥብቆቹም ከእነዚያ ከእናንተ በፊት መጽሐፍን ከተሰጡት ሴቶች ጥብቆቹም፤ ዘማዊዎችና (ዝሙተኞች) የምስጢር ወዳጅ ያዢዎች ሳትኾኑ ጥብቆች ኾናችሁ መህሮቻቸውን በሰጣችኋቸው ጊዜ (ልታገቡዋቸው የተፈቀዱ ናቸው)፡፡ ከእምነትም የሚመለስ ሰው በእርግጥ ሥራው ተበላሸ፡፡ በመጨረሻም ቀን እርሱ ከከሳሪዎቹ ነው፡፡

 • 5:6

  እናንተ ያመናችሁ ሆይ! ወደ ሶላት በቆማችሁ (ለመቆም ባሰባችሁ) ጊዜ ፊቶቻችሁን፣ እጆቻችሁንም እስከ ክርኖች እጠቡ፡፡ ራሶቻችሁንም (በውሃ) አብሱ፡፡ እግሮቻችሁንም እስከ ቁርጭምጭሚቶች (እጠቡ)፡፡ (ሴት ጋር በመገናኘት ወይም በሌላ ምክንያት «ጀናባ») ብትኾኑ (ገላችሁን) ታጠቡ፡፡ በሽተኞች ወይም በጉዞ ላይ ብትኾኑም ወይም ከእናንተ አንዳችሁ ከዓይነ ምድር ቢመጣ ወይም ሴቶችን ብትነካኩና ውሃን ባታገኙ ንጹሕን የምድር ገጽ አስቡ ፡፡ ከሱም ፊቶቻችሁንና እጆቻችሁን አብሱ፡፡ አላህ በእናንተ ላይ ምንም ችግር ሊያደርግ አይሻም፡፡ ግን ታመሰግኑ ዘንድ ሊያጠራችሁና ጸጋውን በእናንተ ላይ ሊሞላ ይሻል፡፡

 • 5:7

  በእናንተም ላይ (የለገሰውን) የአላህን ጸጋ ያንንም ሰምተናል ታዘናልም ባላችሁ ጊዜ በርሱ ያጠበቀባችሁን ቃል ኪዳኑን አስታውሱ፡፡ አላህንም ፍሩ፡፡ አላህ በደረቶች ውስጥ ያለውን ሁሉ ዐዋቂ ነውና፡፡

 • 5:8

  እናንተ ያመናችሁ ሆይ! ለአላህ ቀጥተኞች በትክክል መስካሪዎች ኹኑ፡፡ ሕዝቦችንም መጥላት ባለማስተካከል ላይ አይገፋፋችሁ፡፡ አስተካክሉ፡፡ እርሱ (ማስተካከል) ለአላህ ፍራቻ በጣም የቀረበ ነው፡፡ አላህንም ፍሩ፡፡ አላህ በምትሠሩት ሁሉ ውስጠ ዐዋቂ ነው፡፡

 • 5:9

  እነዚያንም ያመኑትንና በጎ ሥራዎችን የሠሩትን አላህ (ገነትን) ተስፋ አደረገላቸው፡፡ ለእነርሱ ምሕረትና ታላቅ ምንዳ አላቸው፡፡

 • 5:10

  እነዚያም የካዱና በተአምራቶቻችን ያስተባበሉ እነዚያ የእሳት ጓዶች ናቸው፡፡

 • 5:11

  እናንተ ያመናችሁ ሆይ! ሕዝቦች እጆቻቸውን ወደ እናንተ ሊዘረጉ ባሰቡና እጆቻቸውን ከእናንተ ላይ በከለከላችሁ ጊዜ በናንተ ላይ (የዋለላችሁን) የአላህን ጸጋ አስታውሱ፡፡ አላህንም ፍሩ፡፡ ምእመናንም በአላህ ላይ ይመኩ፡፡

 • 5:12

  አላህም የእስራኤልን ልጆች የጠበቀ ቃል ኪዳን በእርግጥ ያዘባቸው፡፡ ከነርሱም ዐስራ ሁለትን አለቆች አስነሳን፡፡ አላህም አላቸው፤ «እኔ ከናንተ ጋር ነኝ፤ ሶላትን ብታስተካክሉ ግዴታ ምጽዋትንም ብትሰጡ በመልክተኞቼም ብታምኑ ብትረዱዋቸውም ለአላህም መልካም ብድርን ብታበድሩ ኀጢአቶቻችሁን ከናንተ በእርግጥ አብሳለሁ፡፡ ከሥሮቻቸው ወንዞች የሚፈሱባቸውን ገነቶችም በእርግጥ አገባችኋለሁ፡፡ ከዚህም በኋላ ከእናንተ የካደ ሰው ቀጥተኛውን መንገድ በእርግጥ ተሳሳተ፡፡»

 • 5:13

  ቃል ኪዳናቸውንም በማፍረሳቸው ረገምናቸው፡፡ ልቦቻቸውንም ደረቆች አደረግን፡፡ ቃላትን ከቦታዎቻቸው ይለውጣሉ፡፡ በርሱም ከታዘዙበት ነገር ፈንታን ተው፡፡ ከእነሱም ጥቂቶች ሲቀሩ ከነርሱ የኾነን ክዳት የምታውቅባቸው ከመኾን አትወገድም፡፡ ከእነርሱም ይቅርታ አድርግ እለፋቸውም፡፡ አላህ መልካም ሠሪዎችን ይወዳልና፡፡

 • 5:14

  ከእነዚያም እኛ ክርስቲያኖች ነን ካሉት የጠበቀ ቃል ኪዳናቸውን ያዝን፡፡ በእርሱም ከታዘዙበት ነገር ፈንታን ተውት፡፡ ስለዚህ እስከ ትንሣኤ ቀን ድረስ በመካከላቸው ጠብንና ጥላቻን ጣልንባቸው፡፡ አላህም ይሠሩት የነበሩትን ሁሉ በእርግጥ ይነግራቸዋል፡፡

 • 5:15

  የመጽሐፉ ባለቤቶች ሆይ! ከመጽሐፉ ትሸሽጉት ከነበራችሁት ነገር ብዙውን ለእናንተ የሚገልጽ ከብዙውም የሚተው ሲኾን መልክተኛችን (ሙሐመድ) በእርግጥ መጣላችሁ፡፡ ከአላህ ዘንድ ብርሃንና ገላጭ መጽሐፍ በእርግጥ መጣላችሁ፡፡

 • 5:16

  አላህ ውዴታውን የተከተሉትን ሰዎች የሰላምን መንገዶች በእርሱ ይመራቸዋል፡፡ በፈቃዱም ከጨለማዎች ወደ ብርሃን ያወጣቸዋል፡፡ ወደ ቀጥተኛም መንገድ ይመራቸዋል፡፡

 • 5:17

  እነዚያ አላህ እርሱ የመርየም ልጅ አልመሲሕ ነው ያሉ በእርግጥ ካዱ፡፡ የመርየምን ልጅ አልመሲሕን እናቱንም በምድር ያለንም ሁሉ ለማጥፋት ቢሻ ከአላህ ማዳንን የሚችል ማነው በላቸው፡፡ የሰማያትና የምድር የመካከላቸውም ንግሥና የአላህ ብቻ ነው፡፡ የሚሻውን ይፈጥራል፡፡ አላህም በነገሩ ሁሉ ላይ ቻይ ነው፡፡

 • 5:18

  አይሁዶችና ክርስቲያኖችም «እኛ የአላህ ልጆችና ወዳጆቹ ነን» አሉ፡፡ «ታዲያ በኃጢአቶቻችሁ ለምን ያሰቃያችኋል አይደላችሁም እናንተ ከፈጠራቸው ሰዎች ናችሁ» በላቸው፡፡ ለሚሻው ሰው ይምራል፡፡ የሚሻውንም ሰው ይቀጣል፡፡ የሰማያትና የምድርም በመካከላቸውም ያለው ሁሉ ንግሥና የአላህ ብቻ ነው፡፡ መመለሻም ወደርሱ ብቻ ነው፡፡

 • 5:19

  እናንተ የመጽሐፉ ሰዎች ሆይ! «አብሳሪና አስፈራሪ አልመጣልንም» እንዳትሉ ከመልክተኞች በመቋረጥ ጊዜ ላይ ሲኾን (ሕጋችንን) የሚያብራራ ኾኖ መልክተኛችን በእርግጥ መጣላችሁ፡፡ አብሳሪና አስፈራሪም በእርግጥ መጣላችሁ፡፡ አላህም በነገሩ ሁሉ ላይ ቻይ ነው፡፡

 • 5:20

  ሙሳም ለሕዝቦቹ ባለ ጊዜ (አስታውስ)፡- «ሕዝቦቼ ሆይ የአላህን ጸጋ በውስጣችሁ ነቢያትን ባደረገና ነገሥታትንም ባደረጋችሁ ከዓለማትም ለአንድም ያልሰጠውን ችሮታ በሰጣችሁ ጊዜ በእናንተ ላይ (ያደረገውን ጸጋ) አስታውሱ፡፡»

 • 5:21

  «ሕዝቦቼ ሆይ! ያችን አላህ ለእናንተ ያደረጋትን የተቀደሰችውን መሬት ግቡ፡፡ ወደ ኋላችሁም አትመለሱ፡፡ ከሳሪዎች ኾናችሁ ትመለሳላችሁና፡፡»

 • 5:22

  «ሙሳ ሆይ! በርስዋ ውስጥ ኀያላን ሕዝቦች አሉ፡፡ ከርስዋም እስከሚወጡ ድረስ እኛ ፈጽሞ አንገባትም፡፡ ከርስዋም ቢወጡ እኛ ገቢዎች ነን» አሉ፡፡

 • 5:23

  ከእነዚያ (አላህን) ከሚፈሩትና አላህ በእነርሱ ላይ ከለገሰላቸው የኾኑ ሁለት ሰዎች «በእነርሱ (በኀያሎቹ) ላይ በሩን ግቡ፡፡ በገባችሁትም ጊዜ እናንተ አሸናፊዎች ናችሁ፡፡ ምእመናንም እንደኾናችሁ በአላህ ላይ ተመኩ» አሉ፡፡

 • 5:24

  «ሙሳ ሆይ! በውስጧ እስካሉ ድረስ እኛ ፈጽሞ ምን ጊዜም አንገባትም፡፡ ስለዚህ ኺድ አንተና ጌታህ ተጋደሉም እኛ እዚህ ተቀማጮች ነን» አሉ፡፡

 • 5:25

  «ጌታዬ ሆይ እኔ ራሴንና ወንድሜን በቀር (ላስገድድ) አልችልም፡፡ በእኛና በአመጸኞቹም ሕዝቦች መካከል ለይ» አለ፡፡

 • 5:26

  እርስዋም (የተቀደሰችው መሬት) በእነርሱ ላይ አርባ ዓመት እርም ናት፡፡ በምድረ በዳ ይንከራተታሉ፡፡ «በአመጸኞችም ሕዝቦች ላይ አትዘን» አለው፡፡

 • 5:27

  በነርሱም ላይ የአደምን ሁለት ልጆች ወሬ ቁርባንን ባቀረቡና (አላህ) ከአንደኛቸው ተቀብሎ ከሌላው ባልተቀበለ ጊዜ (የኾነውን) በእውነት አንብብላቸው፡፡ «በእርግጥ እገድልሃለሁ» አለው፡፡ (ተገዳዩ) «አላህ የሚቀበለው እኮ ከጥንቁቆቹ ብቻ ነው» አለ፡፡

 • 5:28

  «ልትገድለኝ እጅህን ወደኔ ብትዘረጋ እኔ ልገድልህ እጄን ወዳንተ የምዘረጋ አይደለሁም፡፡ እኔ የዓለማትን ጌታ አላህን እፈራለሁና» አለ፡፡

 • 5:29

  «እኔ በኃጢአቴና በኃጢአትህ ልትመለስና ከእሳት ጓዶች ልትኾን እሻለሁ፤ ይኽም የበደለኞች ቅጣት ነው» (አለ)፡፡

 • 5:30

  ነፍሱም ወንድሙን መግደልን ለርሱ ሸለመችለት፤(አነሳሳችው፤)፡፡ ገደለውም፡፡ ከከሳሪዎቹም ኾነ፡፡

 • 5:31

  የወንድሙንም ሬሳ እንዴት እንደሚሸሽግ ያሳየው ዘንድ አላህ መሬትን የሚጭር ቁራን ላከለት፡፡ «ወይ እኔ የወንድሜን ሬሳ እሸሽግ ዘንድ እንደዚህ ቁራ ብጤ መኾን አቃተኝን» አለ፡፡ ከጸጸተኞችም ኾነ፡፡

 • 5:32

  በዚህ ምክንያት በእስራኤል ልጆች ላይ እነሆ ያለ ነፍስ (መግደል) ወይም በምድር ላይ ያለማጥፋት (ካልሆነ በስተቀር) ነፍስን የገደለ ሰው ሰዎቹን ሁሉ እንደገደለ ነው፤ ሕያው ያደረጋትም ሰው ሰዎቹን ሁሉ ሕያው እንዳደረገ ነው ማለትን ጻፍን፡፡ መልክተኞቻችንም በግልጽ ተዓምራት በእርግጥ መጡዋቸው፡፡ ከዚያም ከዚህ በኋላ ከእነሱ ብዙዎቹ በምድር ላይ ወሰንን አላፊዎች ናቸው፡፡

 • 5:33

  የእነዚያ አላህንና መልክተኛውን የሚዋጉ በምድርም ላይ ለማጥፋት የሚተጉ ሰዎች ቅጣት መገደል ወይም መሰቀል ወይም እጆቻቸውንና እግሮቻቸውን በማፈራረቅ መቆረጥ ወይም ከአገር መባረር ነው፡፡ ይህ በነሱ በቅርቢቱ ዓለም ውርደት ነው፡፡ በመጨረሻይቱም ለእነርሱ ከባድ ቅጣት አላቸው፡፡

 • 5:34

  እነዚያ በእነርሱ ላይ ከመቻላችሁ (ከመወሰናችሁ) በፊት የተጸጸቱ ሲቀሩ፡፡ አላህም መሓሪ አዛኝ መኾኑን እወቁ፡፡

 • 5:35

  እናንተ ያመናችሁ ሆይ! አላህን ፍሩ፡፡ ወደርሱም መቃረቢያን (መልካም ሥራን) ፈልጉ፡፡ ትድኑ ዘንድም በእርሱ መንገድ ታገሉ፡፡

 • 5:36

  እነዚያ የካዱት ሰዎች በምድር ላይ ያለው ሁሉ ከእርሱም ጋር ብጤው ከትንሣኤ ቀን ቅጣት በእርሱ ሊበዡበት ለእነርሱ በኖራቸው ኖሮ ከእነሱ ተቀባይን ባላገኙ ነበር፡፡ ለእነሱም አሳማሚ ቅጣት አላቸው፡፡

 • 5:37

  ከእሳት ሊወጡ ይፈልጋሉ፡፡ እነርሱም ከርስዋ ወጪዎች አይደሉም፡፡ ለእነርሱም ዘውታሪ ቅጣት አላቸው፡፡

 • 5:38

  ሰራቂውንና ሰራቂይቱንም በሠሩት ነገር ለቅጣት ከአላህ የኾነን መቀጣጫ እጆቻቸውን ቁረጡ፡፡ አላህም አሸናፊ ጥበበኛ ነው፡፡

 • 5:39

  ከበደሉም በኋላ የተጸጸተና ሥራውን ያሳመረ አላህ ጸጸቱን ከእርሱ ይቀበለዋል፡፡ አላህ መሓሪ አዛኝ ነውና፡፡

 • 5:40

  የሰማያትና የምድር ንግሥና የሱ (የአላህ) ብቻ መኾኑን አላወቅክምን የሚሻውን ሰው ይቀጣል፡፡ ለሚሻውም ሰው ይምራል፡፡ አላህም በነገሩ ሁሉ ላይ ቻይ ነው፡፡

 • 5:41

  አንተ መልክተኛ ሆይ! እነዚያ በክሕደት የሚቻኮሉት ከእነዚያ ልቦቻቸው ያላመኑ ሲኾኑ በአፎቻቸው «አመንን» ካሉትና ከእነዚያም አይሁድ ከኾኑት ሲኾኑ አያሳዝኑህ፡፡ (እነርሱ) ውሸትን አዳማጮች ናቸው፡፡ ለሌሎች ወዳንተ ላልመጡ ሕዝቦች አዳማጮች ናቸው፡፡ ንግግሮችን ከቦታቸው ሌላ ያጣምማሉ፡፡ «ይህንን (የተጣመመውን) ብትስሰጡ ያዙት፡፡ ባትስሰጡትም ተጠንቀቁ» ይላሉ፡፡ አላህም መፈተኑን የሚሻበትን ሰው ለእርሱ ከአላህ (ለመከላከል) ምንንም አትችልም፡፡ እነዚህ እነዚያ አላህ ልቦቻቸውን ማጥራትን ያልሻላቸው ናቸው፡፡ ለእነርሱ በቅርቢቱ ዓለም ውርደት አላቸው፡፡ ለእነርሱም በመጨረሻይቱ ዓለም ከባድ ቅጣት አላቸው፡፡

 • 5:42

  ውሸትን አዳማጮች እርምን በላተኞች ናቸው፡፡ ወደአንተ ቢመጣም በመካከላቸው ፍረድ፡፡ ወይም ተዋቸው፡፡ ብትተዋቸውም ምንም አይጎዱህም፡፡ ብትፈርድም በመካከላቸው በትክክል ፍረድ፡፡ አላህ በትክክል ፈራጆችን ይወዳልና፡፡

 • 5:43

  እነርሱም ዘንድ ተውራት እያለች በውስጧ የአላህ ፍርድ ያለባት ስትኾን እንዴት ያስፈርዱሃል! ከዚያም ከዚህ በኋላ እንዴት ይሸሻሉ! እነዚያም በፍጹም ምእምናን አይደሉም፡፡

 • 5:44

  እኛ ተውራትን በውስጥዋ መምሪያና ብርሃን ያለባት ስትኾን አወረድን፡፡ እነዚያ ትዕዛዝን የተቀበሉት ነቢያት በእነዚያ አይሁዳውያን በኾኑት ላይ በርሷ ይፈርዳሉ፡፡ ሊቃውንቱና ዐዋቂዎቹም ከአላህ መጽሐፍ እንዲጠብቁ በተደረጉትና በርሱም ላይ መስካሪዎች በኾኑት (ይፈርዳሉ)፡፡ ሰዎችንም አትፍሩ፡፡ ፍሩኝም፡፡ በአንቀጾቼም አነስተኛን ዋጋ አትለውጡ፡፡ አላህም ባወረደው ነገር ያልፈረደ ሰው እነዚያ ከሓዲዎቹ እነርሱ ናቸው፡፡

 • 5:45

  በእነርሱም ላይ በውስጧ «ነፍስ በነፍስ ዓይንም በዓይን አፍንጫም በአፍንጫ ጆሮም በጆሮ ጥርስም በጥርስ (ይያዛል)፡፡» ቁስሎችንም ማመሳሰል አለባቸው ማለትን ጻፍን፡፡ በእርሱም የመጸወተ (የማረ) ሰው እርሱ ለርሱ (ለሠራው ኃጢአት) ማስተሰሪያ ነው፡፡ አላህም ባወረደው ነገር የማይፈርድ ሰው፤ እነዚያ በደለኞቹ እነርሱ ናቸው፡፡

 • 5:46

  በፈለጎቻቸውም (በነቢያቶቹ ፈለግ) ላይ የመርየምን ልጅ ዒሳን ከተውራት በስተፊቱ ያለውን አረጋጋጭ ሲኾን አስከተልን፡፡ ኢንጂልንም በውስጡ ቀጥታና ብርሃን ያለበት በስተፊቱ ያለችውን ተውራትንም የሚያረጋግጥ ለጥንቁቆችም መሪና ገሳጭ ሲኾን ሰጠነው፡፡

 • 5:47

  የኢንጅልም ባለቤቶች በውስጡ አላህ ባወረደው ሕግ ይፍረዱ፡፡ አላህም ባወረደው የማይፈርድ ሰው እነዚያ አመጸኞች እነርሱ ናቸው፡፡

 • 5:48

  ወደ አንተም መጽሐፉን ከበፊቱ ያለውን መጽሐፍ አረጋጋጭና በእርሱ ላይ ተጠባባቂ ሲኾን በእውነት አወረድን፡፡ በመካከላቸውም አላህ ባወረደው ሕግ ፍረድ፡፡ እውነቱም ከመጣልህ በኋላ ዝንባሌዎቻቸውን አትከተል፡፡ ከእናንተ ለሁሉም ሕግንና መንገድን አደረግን፡፡ አላህም በሻ ኖሮ አንድ ሕዝብ ባደረጋችሁ ነበር፡፡ ግን በሰጣችሁ ሕግጋት ሊሞክራችሁ (ለያያችሁ)፡፡ በጎ ሥራዎችንም (ለመሥራት) ተሽቀዳደሙ፤ መመለሻችሁ በጠቅላላ ወደ አላህ ነው፡፡ በእርሱም ትለያዩበት የነበራችሁትን ነገር ይነግራችኋል፡፡

 • 5:49

  በመካከላቸውም አላህ ባወረደው ሕግ ፍረድ፡፡ ፍላጎቶቻቸውንም አትከተል፡፡ አላህም ወደ አንተ ካወረደው ከከፊሉ እንዳያሳስቱህ ተጠንቀቃቸው (ማለትን አወረድን)፡፡ ቢዞሩም አላህ የሚሻው በከፊሉ ኃጢአታቸው ሊቀጣቸው መኾኑን ዕወቅ፡፡ ከሰዎቹም ብዙዎቹ አመጸኞች ናቸው፡፡

 • 5:50

  የማይምንነትን ፍርድ ይፈልጋሉን ለሚያረጋግጡም ሰዎች ከአላህ ይበልጥ ፍርዱ ያማረ ማን ነው

 • 5:51

  እናንተ ያመናችሁ ሆይ! አይሁዶችንና ክርስቲያኖችን ረዳቶች አድርጋችሁ አትያዙ፡፡ ከፊላቸው ለከፊሉ ረዳቶች ናቸው፡፡ ከእናንተም ውስጥ ረዳቶች የሚያደርጋቸው ሰው እርሱ ከነርሱ ነው፡፡ አላህ አመጸኞችን ሕዝቦች አያቀናም፡፡

 • 5:52

  እነዚያንም በልቦቻቸው ውስጥ (የንፍቅና) በሽታ ያለባቸውን ሰዎች «የጊዜ መለዋወጥ እንዳያገኘን እንፈራለን የሚሉ» ሲኾኑ በእነርሱ (ለመረዳት) ሲቻኮሉ ታያቸዋለህ፡፡ አላህም ድል መንሳትን ወይም ከእርሱ ዘንድ የኾነን ነገር (ማጋለጥን) ሊያመጣ በነፍሶቻቸው ውስጥ በደበቁትም ነገር ተጸጻቾች ሲሆኑ ተረጋገጠ፡፡

 • 5:53

  እነዚያም ያመኑት ሰዎች፡- «እነዚያ እነርሱ ከእናንተ ጋር ነን ብለው የጠነከረ መሐላቸውን በአላህ የማሉት እነዚህ ናቸውን» ይላሉ፡፡ ሥራዎቻቸው ተበላሹ፡፡ ከሳሪዎችም ኾኑ፡፡

 • 5:54

  እናንተ ያመናችሁ ሆይ! ከእናንተ ውስጥ ከሃይማኖቱ የሚመለስ ሰው አላህ (በእነርሱ ስፍራ) የሚወዳቸውንና የሚወዱትን፣ በምእመናን ላይ ትሑቶች፣ በከሓዲዎች ላይ ኀያላን የኾኑን በአላህ መንገድ የሚታገሉን የወቃሽን ወቀሳ የማይፈሩን ሕዝቦች በእርግጥ ያመጣል፡፡ ይኸ የአላህ ችሮታ ነው፤ ለሚሻው ሰው ይሰጠዋል፤ አላህም ችሮታው ሰፊ ዐዋቂ ነው፡፡

 • 5:55

  ረዳታችሁ አላህና መልክተኛው እነዚያም ያመኑት ብቻ ናቸው፡፡ (እነርሱ) እነዚያ ሶላትን በደንቡ የሚሰግዱ እነርሱም ያጎነበሱ ኾነው ምጽዋትን የሚሰጡ ናቸው፡፡

 • 5:56

  አላህንና መልክተኛውን እነዚያንም ያመኑትን የሚወዳጅ ሰው (ከአላህ ጭፍሮች ይኾናል)፡፡ የአላህም ጭፍሮች እነርሱ አሸናፊዎች ናቸው፡፡

 • 5:57

  እናንተ ያመናችሁ ሆይ! ከእነዚያ ከበፊታችሁ መጽሐፍን ከተሰጡት እነዚያን ሃይማኖታችሁን ማላገጫና መጫወቻ አድርገው የያዙትን ከሓዲዎችንም ረዳቶች አድርጋችሁ አትያዙ፡፡ ምእምናንም እንደኾናችሁ አላህን ፍሩ፡፡

 • 5:58

  ወደ ሶላትም በጠራችሁ ጊዜ (ጥሪይቱን) መሳለቂያና መጫወቻ አድርገው ይይዟታል፡፡ ይህ እነርሱ የማያውቁ ሕዝቦች በመኾናቸው ነው፡፡

 • 5:59

  «የመጽሐፉ ባለቤቶች ሆይ! በአላህና ወደኛ በተወረደው በፊትም በተወረደው ለማመናችን አብዛኞቻችሁም አመጸኞች ለመኾናችሁ እንጅ (ሌላን ነገር) ከኛ ትጠላላችሁን» በላቸው፡፡

 • 5:60

  «አላህ ዘንድ ቅጣቱ ከዚህ የከፋ ነገር ልንገራችሁን» በላቸው፡፡ (እርሱም) «አላህ የረገመው ሰው በእርሱም ላይ ተቆጣበት፡፡ ከእነርሱም ዝንጀሮዎችንና ከርከሮዎችን ያደረገው ጣዖትንም የተገዛ ሰው (ሃይማኖት) ነው፡፡ እነዚያ በጣም በከፋ ስፍራ ናቸው፡፡» ከቀጥተኛውም መንገድ በጣም የተሳሳቱ ናቸው፡፡

 • 5:61

  በመጡዋችሁም ጊዜ (ወደእናንተ) ከክህደት ጋር በእርግጥ የገቡ እነርሱም ከርሱ ጋር በእርግጥ የወጡ ሲኾኑ «አምነናል» ይላሉ፡፡ አላህም ይደብቁት የነበሩትን ነገር በጣም ዐዋቂ ነው፡፡

 • 5:62

  ከእነርሱም ብዙዎቹን በኃጢአትና በበደል እርምንም በመብላታቸው የሚጣደፉ ሲኾኑ ታያለህ፡፡ ይሠሩት የነበሩት ነገር በጣም ከፋ!

 • 5:63

  ቀሳውስቱና ሊቃውንቱ ከኃጢአት ንግግራቸውና እርምን ከመብላታቸው አይከለክሏቸውም ኖሮአልን ይሠሩት የነበሩት ነገር በጣም ከፋ!

 • 5:64

  አይሁዶችም «የአላህ እጅ የታሰረች ናት» አሉ፡፡ እጆቻቸው ይታሰሩ ባሉትም ነገር ይረገሙ፡፡ አይደለም (የአላህ) እጆቹ የተዘረጉ ናቸው፡፡ እንደሚሻ ይለግሳል፡፡ ከጌታህም ወደ አንተ የተወረደው (ቁርኣን) ከእነሱ ብዙዎቹን ትዕቢትንና ክህደትን በእርግጥ ይጨምራቸዋል፡፡ በመካከላቸውም ጠብንና ጥላቻን እስከ ትንሣኤ ቀን ድረስ ጣልን፡፡ ለጦር እሳትን ባያያዙ (ባጫሩ) ቁጥር አላህ ያጠፋታል፡፡ በምድርም ውስጥ ለማበላሸት ይሮጣሉ፡፡ አላህም አበላሺዎችን አይወድም፡፡

 • 5:65

  የመጽሐፉም ባለቤቶች ባመኑና (ከክህደትም) በተጠነቀቁ ኖሮ ከእነሱ ኃጢኣቶቻቸውን በእርግጥ ባበስንና የመጠቀሚያ ገነቶችንም በእርግጥ ባገባናቸው ነበር፡፡

 • 5:66

  እነርሱም ተውራትንና ኢንጂልን ከጌታቸውም ወደእነሱ የተወረደውን መጽሐፍ ባቋቋሙ (በሠሩበት) ኖሮ ከበላያቸውና ከእግሮቻቸው ሥር በተመገቡ ነበር፡፡ ከእነሱ ውስጥ ትክክለኞች ሕዝቦች አልሉ፡፡ ከእነሱም ብዙዎቹ የሚሠሩት ነገር ከፋ!

 • 5:67

  አንተ መልክተኛ ሆይ! ከጌታህ ወዳንተ የተወረደውን አድርስ፡፡ ባትሠራም መልክቱን አላደረስክም፡፡ አላህም ከሰዎች ይጠብቅሃል፡፡ አላህ ከሓዲዎችን ሕዝቦች አያቀናምና፡፡

 • 5:68

  «እናንተ የመጽሐፉ ባለቤቶች ሆይ! ተውራትንና ኢንጂልን ከጌታችሁም ወደእናንተ የተወረደውን እስከምታቆሙ (እስከምትሠሩባቸው) ድረስ በምንም ላይ አይደላችሁም» በላቸው፡፡ ከጌታህም ወደ አንተ የተወረደው ቁርኣን ከእነሱ ብዙዎቹን ትዕቢትንና ክህደትን በእርግጥ ይጨምርባቸዋል፡፡ በከሓዲያን ሕዝቦችም ላይ አትዘን፡፡

 • 5:69

  እነዚያ ያመኑና እነዚያም አይሁዳውያን የኾኑ፣ ሳቢያኖችም፣ ክርስቲያኖችም (ከነርሱ) በአላህና በመጨረሻው ቀን ያመነና መልካምን ሥራ የሠራ ሰው በነርሱ ላይ ፍርሃት የለባቸውም፡፡ እነርሱም አያዝኑም፡፡

 • 5:70

  የእስራኤልን ልጆች የጠበቀ ቃል ኪዳን በእርግጥ ያዝንባቸው፡፡ ወደእነሱም መልክተኞችን ላክን፡፡ ነፍሶቻቸው በማትወደው ነገር መልእክተኛ በመጣላቸው ቁጥር ከፊሉን አስተባበሉ፤ ከፊሉንም ይገድላሉ፡፡

 • 5:71

  ፈተናም አለመኖርዋን ጠረጠሩ፡፡ ታወሩም፣ ደነቆሩም፣ ከዚያም አላህ ከነርሱ ላይ ጸጸትን ተቀበለ፡፡ ከዚያም ከእነሱ ብዙዎቹ ታወሩ፣ ደነቆሩም፡፡ አላህም የሚሠሩትን ሁሉ ተመልካች ነው፡፡

 • 5:72

  እነዚያ «አላህ እርሱ የመርየም ልጅ አልመሲሕ ነው» ያሉ በእርግጥ ካዱ፡፡ አልመሲህም አለ፡- «የእስራኤል ልጆች ሆይ! ጌታዬንና ጌታችሁን አላህን ተገዙ፡፡» እነሆ! በአላህ የሚያጋራ ሰው አላህ በርሱ ላይ ገነትን በእርግጥ እርም አደረገ፡፡ መኖሪያውም እሳት ናት፡፡ ለበዳዮችም ምንም ረዳቶች የሏቸውም፡፡

 • 5:73

  እነዚያ «አላህ የሦስት ሦስተኛ ነው» ያሉ በእርግጥ ካዱ፡፡ ከአምላክም አንድ አምላክ እንጅ ሌላ የለም፡፡ ከሚሉትም ነገር ባይከለከሉ ከነሱ እነዚያን የካዱትን አሳማሚ ቅጣት በእርግጥ ይነካቸዋል፡፡

 • 5:74

  ወደ አላህ አይመለሱምና ምሕረትን አይለምኑትምን አላህም መሓሪ አዛኝ ነው፡፡

 • 5:75

  የመርየም ልጅ አልመሲሕ ከበፊቱ መልክተኞች በእርግጥ ያለፉ የኾነ መልክተኛ እንጅ ሌላ አይደለም፡፡ እናቱም በጣም እውነተኛ ናት፡፡ (ሁለቱም) ምግብን የሚበሉ ነበሩ፤ አንቀጾችን ለነርሱ (ለከሓዲዎች) እንዴት እንደምናብራራ ተመልከት ከዚያም (ከእውነት) እንዴት እንደሚመለሱ ተመልከት፡፡

 • 5:76

  «ከአላህ ሌላ ለእናንተ መጉዳትንና መጥቀምን የማይችልን ትገዛላችሁን» በላቸው፡፡ አላህም እርሱ ሰሚው ዐዋቂ ነው፡፡

 • 5:77

  «እናንተ የመጽሐፉ ባለቤቶች ሆይ! በሃይማኖታችሁ ከእውነት ሌላ የኾነን (ማለፍ) ወሰንን አትለፉ፡፡ በፊትም በእርግጥ የተሳሳቱትንና ከቀጥተኛው መንገድም (አሁን) የተሳሳቱን ሕዝቦች ከንቱ ዝንባሌዎች አትከተሉ» በላቸው፡፡

 • 5:78

  ከእስራኤል ልጆች እነዚያ የካዱት በዳውድና በመርየም ልጅ በዒሳ ምላስ ተረገሙ፡፡ ይህ ትእዛዝን በመጣሳቸውና ወሰንን የሚያልፉ በመኾናቸው ነው፡፡

 • 5:79

  ከሠሩት መጥፎ ነገር አይከላከሉም ነበር፡፡ ይሠሩት የነበሩት ነገር በእርግጥ ከፋ!

 • 5:80

  ከእነሱ ብዙዎቹን እነዚያን የካዱትን ሲወዳጁ ታያለህ፡፡ በእነሱ ላይ አላህ የተቆጣባቸው በመኾኑ ለእነርሱ ነፍሶቻቸው ያስቀደሙት ሥራ በጣም ከፋ፡፡ እነሱም በቅጣት ውስጥ ዘውታሪዎች ናቸው፡፡

 • 5:81

  በአላህና በነቢዩ ወደርሱም በተወረደው ቁርኣን የሚያምኑ በኾኑ ኖሮ ወዳጆች አድርገው ባልያዙዋቸው ነበር፡፡ ግን ከነርሱ ብዙዎቹ አመጠኞች ናቸው፡፡

 • 5:82

  አይሁዶችንና እነዚያን ያጋሩትን ለእነዚያ ለአመኑት በጠላትነት ከሰዎች ሁሉ ይበልጥ የበረቱ ኾነው በእርግጥ ታገኛለህ፡፡ እነዚያንም «እኛ ክርስቲያኖች ነን» ያሉትን ለእነዚያ ለአመኑት በወዳጅነት በእርግጥ ይበልጥ የቀረቧቸው ኾነው ታገኛለህ፡፡ ይህ ከእነሱ ውስጥ ቀሳውስትና መነኮሳት በመኖራቸውና እነሱም የማይኮሩ በመኾናቸው ነው፡፡

 • 5:83

  ወደ መልክተኛውም የተወረደውን (ቁርኣን) በሰሙ ጊዜ እውነቱን ከማወቃቸው የተነሳ ዓይኖቻቸው እንባን ሲያፈሱ ታያለህ፡፡ «ጌታችን ሆይ! አመንን ከመስካሪዎቹም ጋር ጻፈን » ይላሉ፡፡

 • 5:84

  «በአላህና ከውነትም በመጣልን ነገር የማናምን ጌታችንም ከመልካም ሰዎች ጋር ሊያስገባን የማንከጅል ለኛ ምን አለን» (ይላሉ)፡፡

 • 5:85

  ባሉትም ምክንያት አላህ በስሥሮቻቸው ወንዞች የሚፈሱባቸውን ገነቶች በውስጣቸው ዘውታሪዎች ሲኾኑ መነዳቸው፡፡ ይህም የበጎ ሠሪዎች ዋጋ ነው፡፡

 • 5:86

  እነዚያም የካዱና በአንቀጾቻችን ያስተባበሉ እነዚያ የእሳት ጓዶች ናቸው፡፡

 • 5:87

  እናንተ ያመናችሁ ሆይ! አላህ ለናንተ የፈቀደላችሁን ጣፋጮች እርም አታድርጉ፡፡ ወሰንንም አትለፉ፡፡ አላህ ወሰን አላፊዎችን አይወድምና፡፡

 • 5:88

  አላህም ከሰጣችሁ ሲሳይ የተፈቀደ ጣፋጭ ሲኾን ብሉ፡፡ ያንንም እናንተ በርሱ አማኞች የኾናችሁበትን አላህን ፍሩ፡፡

 • 5:89

  አላህ በመሐላዎቻችሁ በውድቁ አይዛችሁም፡፡ ግን መሐላዎችን (ባሰባችሁት) ይይዛችኋል፡፡ ማስተሰሪያውም ቤተሰቦቻችሁን ከምትመግቡት ከመካከለኛው (ምግብ) ዐስርን ምስኪኖች ማብላት ወይም እነሱን ማልበስ ወይም ጫንቃን ነጻ ማውጣት ነው፤ (ከተባሉት አንዱን) ያላገኘም ሰው ሦስት ቀኖችን መጾም ነው፤ ይህ በማላችሁ ጊዜ የመሐላዎቻችሁ ማካካሻ ነው፡፡ መሐላዎቻችሁንም ጠብቁ፡፡ እንደዚሁ አላህ ለናንተ አንቀጾችን ያብራራል፡፡ እናንተ ልታመሰግኑ ይከጀላልና፡፡

 • 5:90

  እናንተ ያመናችሁ ሆይ! የሚያሰክር መጠጥ ቁማርም ጣዖታትም አዝላምም ከሰይጣን ሥራ የኾኑ እርኩስ ብቻ ናቸው፡፡ (እርኩስን) ራቁትም ልትድኑ ይከጀላልና፡፡

 • 5:91

  ሰይጣን የሚፈልገው በሚያሰክር መጠጥና በቁማር በመካከላችሁ ጠብንና ጥላቻን ሊጥል አላህን ከማውሳትና ከስግደትም ሊያግዳችሁ ብቻ ነው፡፡ ታዲያ እናንተ (ከእነዚህ) ተከልካዮች ናችሁን (ተከልከሉ)፡፡

 • 5:92

  አላህንም ተገዙ፡፡ መልክተኛውንም ታዘዙ፡፡ ተጠንቀቁም፡፡ ብትሸሹም፤ በመልክተኛችን ላይ ያለበት ግልጽ ማድረስ ብቻ መኾኑን ዕወቁ፡፡

 • 5:93

  በእነዚያ ባመኑትና በጎ ሥራዎችን በሠሩት ላይ (ክህደትን) በተጠነቀቁና ባመኑ መልካም ሥራዎችንም በሠሩ ከዚያም (የሚያሰክርንና ቁማርን) በተጠነቀቁና ባመኑ ከዚያም (ከተከለከለው ሁሉ) በተጠነቀቁና (ሥራን) ባሳመሩ ጊዜ (ከመከልከሉ በፊት) በተመገቡት ነገር ኃጢአት የለባቸውም፡፡ አላህም በጎ ሠሪዎችን ይወዳል፡፡

 • 5:94

  እናንተ ያመናችሁ ሆይ! (በሐጅ ጊዜ) እጆቻችሁና ጦሮቻችሁ በሚያገኙት ታዳኝ አውሬ አላህ ይሞክራችኋል፡፡ በሩቅ ኾኖ የሚፈራውን ሰው አላህ ሊገልጽ (ይሞክራችኋል)፡፡ ከዚያም በኋላ ወሰንን ያለፈና ያደነ ሰው ለርሱ አሳማሚ ቅጣት አለው፡፡

 • 5:95

  እናንተ ያመናችሁ ሆይ! እናንት በሐጅ ሥራ ውስጥ ስትኾኑ አውሬን አትግደሉ፡፡ ከእናንተም እያወቀ የገደለው ሰው ቅጣቱ ከእናንተ ሁለት የትክክለኛነት ባለቤቶች የሚፈርዱበት የኾነ ወደ ካዕባ ደራሽ መሥዋዕት ሲኾን ከቤት እንስሳዎች የገደለውን ነገር ብጤ መስጠት ወይም ምስኪኖችን ማብላት ወይም የዚህን ልክ መጾም ማካካሻ ነው፡፡ (ይኽም) የሥራውን ከባድ ቅጣት እንዲቀምስ ነው፡፡ (ሳይከለከል በፊት) ካለፈው ነገር አላህ ይቅርታ አደረገ፡፡ (ወደ ጥፋቱም) የተመለሰም ሰው አላህ ከርሱ ይበቀላል፡፡ አላህም አሸናፊ የመበቀል ባለቤት ነው፡፡

 • 5:96

  የባሕር ታዳኝና ምግቡ ለእናንተም ለመንገደኞችም መጠቀሚያ ይኾን ዘንድ ለናንተ ተፈቀደ፡፡ በሐጅም ላይ እስካላችሁ ድረስ የየብስ አውሬ በናንተ ላይ እርም ተደረገ፡፡ ያንንም ወደርሱ የምትሰበሰቡበትን አላህን ፍሩ፡፡

 • 5:97

  ከዕባን፣ የተከበረውን ቤት፣ ክልክል የኾነውንም ወር፣ መስዋዕቱንና ባለ ምልክቶቹንም መንጋዎች አላህ ለሰዎች መቋቋሚያ አደረገ፡፡ ይህ አላህ በሰማያት ያለውን ሁሉ በምድርም ያለውን ሁሉ የሚያውቅ መኾኑን አላህም ነገሩን ሁሉ ዐዋቂ መኾኑን እንድታውቁ ነው፡፡

 • 5:98

  አላህ ቅጣተ ብርቱ መኾኑን አላህም መሓሪ አዛኝ መኾኑን እወቁ፡፡

 • 5:99

  በመልክተኛው ላይ ማድረስ እንጅ ሌላ የለበትም፡፡ አላህም የምትገልጹትን ነገር የምትደብቁትንም ሁሉ ያውቃል፡፡

 • 5:100

  «የመጥፎው (ገንዘብ) ብዛት ቢያስደንቃችሁም እንኳ መጥፎውና ጥሩው አይስተካከሉም፡፡ ባለልቦች ሆይ! አላህንም ፍሩ፤ እናንተ ልትድኑ ይከጀላልና፤» በላቸው፡፡

 • 5:101

  እናንተ ያመናችሁ ሆይ! ለእናንተ ቢገለጹ ከሚያስከፏችሁ ነገሮች አትጠይቁ፡፡ ቁርኣንም በሚወርድበት ጊዜ ከእርሷ ብትጠይቁ ለናንተ ትገለጻለች፤ ከእርሷ አላህ ይቅርታ አደረገ፡፡ አላህም መሓሪ ታጋሽ ነው፡፡

 • 5:102

  ከናንተም በፊት ሕዝቦች በእርግጥ ጠየቋት፡፡ ከዚያም በእርሷ (ምክንያት) ከሓዲዎች ኾኑ፡፡

 • 5:103

  ከበሒራ ከሳኢባም ከወሲላም ከሓምም አላህ ምንንም (ሕግ) አላደረገም፡፡ ግን እነዚያ የካዱት በአላህ ላይ ውሸትን ይቀጣጥፋሉ፡፡ አብዛኞቻቸውም አያውቁም፡፡

 • 5:104

  ለእነርሱም አላህ ወደ አወረደውና ወደ መልክተኛው ኑ በተባሉ ጊዜ «አባቶቻችንን በርሱ ላይ ያገኘንበት ነገር ይበቃናል» ይላሉ፡፡ አባቶቻቸው ምንም የማያውቁና የማይመሩ ቢኾኑም (ይኸንን ማለት ይበቃቸዋልን)

 • 5:105

  እናንተ ያመናችሁ ሆይ! ነፍሶቻችሁን (ከእሳት) ያዙ፤ (ጠብቁ)፡፡ በተመራችሁ ጊዜ የተሳሳተ ሰው አይጎዳችሁም፡፡ የሁላችሁም መመለሻ ወደ አላህ ብቻ ነው፡፡ ትሠሩትም የነበራችሁትን ሁሉ ይነግራችኋል፡፡

 • 5:106

  እናንተ ያመናችሁ ሆይ! አንዳችሁን ሞት በመጣበት ጊዜ በኑዛዜ ወቅት የመካከላችሁ ምስክርነት ከእናንተ ሁለት የትክክለኛነት ባለቤቶች የኾኑ ሰዎች ወይም በምድር ብትጓዙና የሞት አደጋ ብትነካችሁ ከሌሎቻችሁ የኾኑ ሁለት ሌሎች ሰዎች (መመስከር) ነው፡፡ ብትጠራጠሩ ከሶላት (ከዐሱር) በኋላ ታቆሟቸውና (የሚመሰክርለት ሰው) የዝምድና ባለቤት ቢኾንም እንኳ «በርሱ ዋጋን አንገዛም የአላህንም ምስክርነት አንደብቅም፤ ያን ጊዜ (ደብቀን ብንገኝ) እኛ ከኃጢአተኞች ነን» ብለው በአላህ ስም ይምላሉ፡፡

 • 5:107

  እነርሱም ኃጢአትን (በውሸት መስክረው) የተገቡ መኾናቸው ቢታወቅ ከእነዚያ (ለሟቹ) ቅርቦች በመኾን (ውርስ) ከተገባቸው የኾኑ ሁለት ሌሎች ሰዎች በስፍራቸው (በምስክሮች ስፍራ) ይቆሙና «ምስክርነታችን ከእነሱ ምስክርነት ይልቅ እውነት ነው ወሰንም አላለፍንም ያን ጊዜ እኛ ከበዳዮች ነን» ሲሉ በአላህ ይምላሉ፡፡

 • 5:108

  ይህ ምስክርነትን በተገቢዋ ላይ ለማምጣታቸው ወይም ከመሐላዎቻቸው በኋላ የመሐላዎችን (ወደ ወራሾች) መመለስን ለመፍራት በጣም የቀረበ ነው፡፡ አላህንም ፍሩ፡፡ ስሙም፡፡ አላህም አመጸኞች ሕዝቦችን አይመራም፡፡

 • 5:109

  አላህ መልክተኞቹን የሚሰበስብበትንና «ምን መልስ ተሰጣችሁ» የሚልበትን ቀን (አስታውስ)፡፡ «ለእኛ ምንም ዕውቀት የለንም አንተ ሩቆችን በጣም ዐዋቂ አንተ ብቻ ነህ» ይላሉ፡፡

 • 5:110

  አላህ በሚል ጊዜ (አስታውስ)፡- «የመርየም ልጅ ዒሳ ሆይ! በአንተና በእናትህ ላይ (የዋልኩላችሁን) ጸጋዬን አስታውስ፡፡ በሕፃንነትና በከፈኒሳነት (የበሰለ ሰው ኾነህ) ሰዎችን የምትናገር ስትኾን በቅዱስ መንፈስ (በገብሬል) ባበረታሁህ ጊዜ፤ ጽሕፈትንና ጥበብንም ተውራትንና ኢንጂልንም ባስተማርኩህ ጊዜ፣ ከጭቃም የወፍ ቅርጽ ብጤ በፈቃዴ በምትሠራና በውስጧ በምትነፋ በፈቃዴም ወፍ በምትኾን ጊዜ፣ ዕውርም ኾኖ የተወለደንና ለምጻምንም በፈቃዴ በምታሽር ጊዜ፣ ሙታንንም በፈቃዴ (ከመቃብራቸው) በምታወጣ ጊዜ፣ የእስራኤልንም ልጆች በተአምራት በመጣህባቸውና ከእነሱ እነዚያ የካዱት ይህ ግልጽ ድግምት እንጅ ሌላ አይደለም ባሉ ጊዜ፣ (ሊገድሉህ ሲያስቡህ) ከአንተ ላይ በከለከልኩልህም ጊዜ (ያደረግሁልህን ውለታ አስታውስ)፡፡»

 • 5:111

  ወደ ሐዋርያትም «በኔና በመልክተኛዬ እመኑ» በማለት ባዘዝኩ ጊዜ (አስታውስ)፡፡ «አመንን፤ እኛ ሙስሊሞች መኾናችንን መስክር» አሉ፡፡

 • 5:112

  ሐዋርያት፡- «የመርየም ልጅ ዒሳ ሆይ! ጌታህ በእኛ ላይ ከሰማይ ማእድን ሊያወርድልን ይችላልን» ባሉ ጊዜ (አስታውስ)፡፡ «ምእመናን እንደ ኾናችሁ አላህን ፍሩ» አላቸው፡፡

 • 5:113

  «ከእርሷ ልንበላ ልቦቻችንም ሊረኩ እውነት ያልከንም መኾንህን ልናውቅና በእርሷም ላይ ከመስካሪዎች ልንኾን እንፈልጋለን» አሉ፡፡

 • 5:114

  የመርየም ልጅ ዒሳ አለ፡- «ጌታችን አላህ ሆይ! ለእኛ ለመጀመሪያዎቻችንና ለመጨረሻዎቻችን ባዕል (መደሰቻ) የምትኾንን ከአንተም ተአምር የኾነችን ማእድ ከሰማይ በእኛ ላይ አውርድ፡፡ ስጠንም፡፡ አንተ ከሰጪዎች ሁሉ በላጭ ነህና፡፡»

 • 5:115

  አላህ፡- «እኔ (ማእድዋን) በናንተ ላይ አውራጅዋ ነኝ፡፡ በኋላም ከእናንተ የሚክድ ሰው እኔ ከዓለማት አንድንም የማልቀጣውን ቅጣት እቀጣዋለሁ» አለ፡፡

 • 5:116

  አላህም፡- «የመርየም ልጅ ዒሳ ሆይ! አንተ ለሰዎቹ፡- እኔንና እናቴን ከአላህ ሌላ ሁለት አምላኮች አድርጋችሁ ያዙ ብላሃልን» በሚለው ጊዜ (አስታውስ)፡፡ «ጥራት ይገባህ፤ ለእኔ ተገቢዬ ያልኾነን ነገር ማለት ለኔ አይገባኝም፡፡ ብዬው እንደ ኾነም በእርግጥ ዐውቀኸዋል፡፡ በነፍሴ ውስጥ ያለውን ሁሉ ታውቃለህ፡፡ ግን አንተ ዘንድ ያለውን አላውቅም፡፡ አንተ ሩቆችን ሁሉ በጣም ዐዋቂ አንተ ብቻ ነህና» ይላል፡፡

 • 5:117

  «በእርሱ ያዘዝከኝን ቃል ጌታዬንና ጌታችሁን አላህን ተገዙ ማለትን እንጂ ለነርሱ ሌላ አላልኩም፡፡ በውስጣቸውም እስካለሁ ድረስ በነርሱ ላይ ተጣባበቂ ነበርኩ፡፡ በተሞላኸኝም ጊዜ (ባነሳኸኝ ጊዜ) አንተ በነሱ ላይ ተጠባባቂ ነበርክ፡፡ አንተም በነገሩ ሁሉ ላይ ዐዋቂ ነህ፡፡»

 • 5:118

  «ብትቀጣቸው እነርሱ ባሮችህ ናቸው፡፡ ለነርሱ ብትምርም አንተ አሸናፊው ጥበበኛው ነህ» (ይላል)፡፡

 • 5:119

  አላህ ይላል፡- «ይህ እውነተኞችን እውነታቸው የሚጠቅምበት ቀን ነው፡፡ ለእነርሱ በሥሮቻቸው ወንዞች የሚፈሱባቸው በውስጣቸው ሁልጊዜ ዘውታሪዎች ሲኾኑ የሚኖሩባቸው ገነቶች አሉዋቸው፡፡ አላህ ከእነሱ ወደደ፤ እነርሱም ከእርሱ ወደዱ፤ ይህ ታላቅ ዕድል ነው፡፡»

 • 5:120

  የሰማያትና የምድር በውስጣቸውም ያለው ሁሉ ንግሥና የአላህ ብቻ ነው፡፡ እሱም በነገሩ ሁሉ ላይ ቻይ ነው፡፡

Paylaş
Tweet'le